የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቀድሞ በደቡብ ብሔር፤ ብሔረሠቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት አካል የነበሩና የህዝቦችን ጥያቄና ፍላጎት መሰረት አድርገው በአዲሱ ከተደራጁት የሲዳማ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ክልሉ የኢፌድሪ ህገመንግስት በሚፈቅደው የክልሎች አደረጃጀት መሰረት በስሩ 12 ዞኖችን እና 95 ወረዳዎችን ይዞ የተቋቋመ ክልል ነው፡፡
የመንግስት አደረጃጀቱም የህዝቦችን መብቶችና የመልካም አስተዳደር ፍላጎቶች ለሟሟላት በሚያስችል መልኩ የህግ አውጭ፤ የህግ ተርጓሚና አስፈጻሚ አካላት ያሉት ሲሆን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲሁም የመንግስት አገልግሎቶች ተደራሽነት ይረጋገጥ ዘንድ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በስድስት ብዝሃ-ማዕከላት ወላይታ-ሶዶ የክልሉ የፖለቲካና የአስተዳደር ዋና ማእከል፤ እንዲሁም አርባ ምንጭ የህግ አውጭና የኢኮኖሚ ክላስተር ማእከል፣ ሳውላ የህግ ተርጓሚና የፍትህ ተቋማት ክላስተር ማእከል፣ ካራት የህገመንግስት ትርጉም ማእከል፣ ጂንካ የማህበራዊ ክላስተር ማእከል እና ዲላ የግብርናና የገጠር ልማት ተቋማት ማእከል በመሆን እንዲደራጁ ተደርጓል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አኩሪ ባህል፤ ታሪክና መልክአ ምድራዊ አሰፋፈር፤ የስነ ልቦና አንድነት፤ በጋራ ያፈራው ጥቅምና የመልማት ፍላጎት ያለው እንዲሁም ጠንካራ የእርስ በእርስ ትስስር ያላቸው 32 ነባር ብሄረሰቦችንና ሌሎች የሀገራችንን ብሄሮችና ህዝቦችን በጋራ ይዞ የመሰረተ ክልል ነው፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መመስረት መሠረታውያን የህዝብ ህገ-መንግስታዊ በክልል የመደራጀት መብት፤ የክልሉ ህዝብ ጥያቄና ፍላጎት፣ የመልካም አስተዳደርና የልማት ፍላጎቶች እየጨመሩ መምጣት፣ የመንግስት አገልግሎቶች ፍትሃዊ ተደራሽነት የማረጋግጥ መንግስታዊ ግዴታ፤ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ፍላጎት፣ የህዝቦችን የእርስ በእርስ ትስስርን የማጎልበት፤ የተለያዩ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን የመፍታት፤ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት በመጠቀም ቋንቋን፤ ባህልንና አንድነትን የማጠናከር፤ እምቅ የተፈጥሮ ሀብትን በተሻለ አደረጃጀትና አሰተዳደር ለጋራ ጥቅም የማዋል፤ የህግ በላይነትንና ዴሞክራሲን የማስፈን፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገቶችን የማፍጠን ወዘተ… ናቸው፡፡ በእነዚህና በሌሎችም መሠረታዊ ጉዳዮች ምክንያት የተሻሉ እድሎችን ይዞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በነሀሴ 12 ቀን 2015 ዓ.ም በይፋ ተመስርቷል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ስር በአዋጅ ቁጥር 01/ የ2015 መሰረት ከተቋቋሙት ተቋማት ውስጥ አንዱ ነው፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ተቋም የመንግስት ፖሊሲዎችን፣ ፕሮግራሞችን፤ አጀንዳዎችን ወዘተ… አፈፃፀማቸውን በተቀናጀና በተናበበ እንዲሁም ውጤታማ በሆነ አኳኋን ለዜጎች ተደራሽ በማድረግ ዜጎች በሀገራዊ የልማት ጉዳዮች ተካታች ሆነው በብቃት እንዲሳተፉ በማድረግ ዋና ዋና ሀገራዊ የመንግስት ግቦች በሚጠበቀው ፍጥነትና ጥራት እንዲፈጸሙ እንዲያስችል የተቀረጸ የመንግስት መዋቅር ነው፡፡
ተቋሙ ዘመኑ የደረሰበትን የዲጂታል ሚዲ በሰፊው በመጠቀም የሬዲዮና የቴሌቪዥን ዜናችንና ፕሮግራሞችን በዌብሳይት፤ በቴሌግራም፤ በቲውተር እና ሌሎች የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም መረጃን በተቀላጠፈ መልኩ ለህዝብ የሚያደርስ ተቋም ነው፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሴክተር የክልሉ ሕዝቦች ህብረ-ብሔራዊ አንድነታቸውን ጠብቀው በክልሉ ሁለንተናዊ ልማት በብቃት እንዲሳተፉ በማድረግ አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት በሚደረግ የክልሉ መንግስት ጥረት ውስጥ የሚጠበቅበትን ተቋማዊ ተልዕኮ ለመፈጸም በመደራጀት፤ ጠንካራና ውጤታማ የኮሚዩኒኬሽን ስርአት በመዘርጋትና ስትራቴጂካዊ ጉዳዮችን በመለየት የሚንቀሳቀስ ተቋም ነው፡፡
እነዚህን ክልልዊና ሀገራዊ ትላልቅ ስራዎችን በብቃትና በጥራት ይፈጽም ዘንድ ግልጽና የተቋሙን መዳረሻ እንዲሁም አሰራርና አቅሙን የሚያሣይ ራዕይና ተልእኮ፤ ኃላፊነትና ተግባራት የተቀረጹለት ተቋም ነው፡፡
ተልዕኮ
ሁሉ አቀፍና አዳዲስ የኮሚዩኒኬሽን መገናኛ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለህብረተሰቡ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶችን እንዲሁም የኢንቨስትመንት መረጃዎችን የሚሰጥ በመረጃ የበለጸገ ህብረተሰብን የሚፈጥርና የክልሉን ገጽታ የሚገነባ በጥናትና ምርምር የታገዘ አካታች የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የኮሚዩኒኬሽን ስርዓትና ምቹ ከባቢ መፍጠር ነው፡፡
ራዕይ
በ2022 ዓ.ም በመረጃ የበለጸገ እና በሀገሩ ላይ መልካም ገጽታን የተጎናጸፈ ዜጋ ተፈጥሮ ማየት፤
ስልጣንና ተግባር
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በህግ የተሰጡት የሚከተሉት ስልጣንና ተግባራት አሉት፡-
1. የክልሉን መንግስት እና የርዕሰ መስተዳድሩ ቃል አቀባይ ሆኖ ያገለግላል፤
2) የክልሉን መንግስት ኢንፎርሜሽን በማእከል አደራጅቶ ለሚመለከታቸው አካላት እና ለሚዲያ እንደአስፈላጊነቱ ያሰራጫል፤
3) የክልሉ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ሴክተር መስሪያ ቤቶች የህዝብ ግንኙነት ስራዎች ያስተባብራል፤
4) የክልሉ ማእከል ሴክተር መስሪያ ቤቶችን የኮምዩኒኬሽንና የሚዲያ ግንኙነት ስራ ያስተባብራል፤
5) የክልሉን መንግስት የህዝብ ግንኙነት ስራዎች ያከናውናል፤ ኮንፈረንሶች፤ ፓናል ውይይቶችን እና ሁነቶችን ያደራጃል፤
6) የክልሉን ርዕሰ መስተዳደር እና መንግስት የሚዲያ ግንኙነት ስራ ያከናውናል፤
7) የሚዲያ ሞኒተሪንግ እና ትንታኔ ስራ እያከናወነ መረጃውን ለርዕሰ መስተዳደሩ እና እንደአስፈላጊነቱ ለሚመለከታቸው አካላት ያስተላልፋል፤
8) የሚዲያ አዝማሚያ ጥናት ያከናውናል፤ ሪፖርት አዘጋጅቶ ለርዕሰ መስተዳደሩ እና እንደአስፈላጊነታቸው ለሚመለከታቸው አካላት ያተላልፋል፤
9) ቤወቅቱ ህዝብን በሚያሳስቡ ጉዳዮች ላይ ዕለታዊ እና ሳምንታዊ የህዝብ አስተያየት መረጃዎችን ያሰባስባል፤ ለርዕሰ መስተዳደሩ እና እንደአስፈላጊነታቸው ለሚመለከታቸው አካላት ያስተላልፋል፤
10) በትላልቅ የህዝብ እና የመንግስት ጉዳዮች እና ፖሊሲዎች ላይ የህዝብ አመለካካት ጥናት ያከናውናል፤ ለሚመለከታቸው አከላት ያቀርባል፤
11) የክልሉን መንግስት መረጃ፤ ኢንፎርሜሽንና መልእክት በቋሚነት ያሰራጫል፤
12) የክልሉን ኢንፎርሜሽን እና ኮምዩኒኬሽን ስራ ከፌደራል መንግስት ስራ ጋር የሚያቀናጅ የስራ ግንኙነት እና ትብብር ይፈጥራል፤ ያፈጽማል፤
13) አገራዊ እና ክልላዊ የኢንፎርሜሽን፤ የኮምዩኒኬሽን እና የሚዲያ ሴክተር ፖሊሲዎች እና ሕጎች በክልሉ መተግበሩን ይከታተላል፤
14) የፌደራል የማስታወቂያ ህጎችን መሰረት በማድረግ የማስታወቂያ ስራ ብቃት ማረጋገጫ ይሰጣል፤ይከታተላል፤
15) የክልሉን ገጽታ ግንባታ ተግባራትን ያከናውናል፤
16) ዓለማውን ለማስፈጻም የሚረዱ ሌሎች ተግባራትን ያከናውናል፤
የሚሰጡ ዋና ዋና አገልግሎቶች
----//////---
Copyrights 2021. . All Rights Reserved.
Developed by NATNAEL ABATE