የህዝባችንን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ገቢን በተቀናጀ አግባብ አሟጦ መሰብሰብ የአመራሩ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል፦ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
የህዝባችንን ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፥ ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ፍትሃዊ ገቢን በተቀናጀ አግባብ አሟጦ መሰብሰብ የአመራሩ ቀዳሚ ተግባር እና ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ መልዕክት አስተላለፉ። የክልሉ መንግሥት ፍትሀዊ ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ የህዝቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች እና አዳጊ የመልማት ፍላጎቶች ደረጃ በደረጃ በመመለስ ዳግም ቃልን በተግባር ለማረጋገጥ በትኩረት በመስራት ላይ ሲሆን፥ በሂደቱ ግዴታቸውን በማይወጡ በየደረጃው ያሉ የገቢ ዘርፍ አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና ግብር ከፋዮች ላይ ህግ የማስከበር እርምጃዎችን በቁርጠኝነት የሚወስድ ይሆናል ሲሉም ተናግረዋል።
የክልሉን ገቢ ለማሳደግ የህግ ማዕቀፍ የማሻሻል፣ የድጂታል አሰራር ስርዓት ተደራሽ በማድረግ የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን የማዘመን፣ ግብር የሚሰውሩ አካላትን ህጋዊ መስመር የማስያዝ፣ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን የመከላከልና ሌሎች የማሻሻያ ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን፥ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ሲሉም ገልፀዋል።
ለሰነቅናቸው የልማትና የብልፅግና ራዕዮች ስኬት፤ በየደረጃው የውስጥ አቅምን በማጎልበት በራስ አቅም የልማት ጥያቄዎችን በብቃት ለመመለስና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስራት ለነገ የማይባል፤ ለአንድ ወገን የማይተው ተግባር መሆኑን በመገንዘብ አመራሩ፥ ባለሞያው፥ የሕዝብ እንደራሴዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በጋራ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባችኋል በማለት ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
ግብር ከፋዩም የህብረተሰብ ክፍል የሚጠበቅበትን የገቢ ግብር በወቅቱ በታማኝነት በመክፈልና ማህበራዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ በመወጣት የልማት አጋርነቱን በተግባር ሊያስመሰክር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በህብረት ሁለንተናዊ ብልፅግናችንን በጋራ ጥረትና ትጋት እናረጋግጣለን!!
ፈጣሪ ሀገራችንንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
Copyrights 2021. . All Rights Reserved.
Developed by NATNAEL ABATE