• Call Us
  • +251..........

ከ348 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የዲላ ከተማ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመረቀ

ከ348 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የዲላ ከተማ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመረቀ 

ፕሮጀክቱ ከ192 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተመላክቷል 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ፕሮጀክቱ የከተማውን ደረጃ ከፍ ከማድረጉ ባሻገር ብልፅግና ፓርቲ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የመጨረስ ባህሉን በተግባር የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል። 

የዲላ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለህብረተሰቡ ከመጠጥ ውሃ ባሻገር የሳንቴሽን አገልግሎትም የሚሰጥ በመሆኑ ህብረተሰቡ ሊጠብቀው ይገባል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አመላክተዋል። 

በርካታ የመንግስት በጀት የወጣበትን ፕሮጀክት ያለማቋረጥ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ የዲላ ከተማ የውሃ አገልግሎት ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለው የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግስት የሚጠበቅበትን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል። 

ለፕሮጀክቱ መጠናቀቅ የድርሻቸውን የተወጡ አካላትን ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ አመስግነዋል። 

የኢፌዴሪ ውሃና ኢነርጂ  ሚኒስቴር ሚኒስትር  ዶክተር ኢንጂነር ሐብታሙ ኢተፋ በመርሃ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት የፌደራል መንግስት በሀገሪቱ እየተስተዋለ የሚገኘውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል። 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በ8 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወጪ የተለያዩ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ እንደሚገኙም ሚኒስትሩ አብራርተዋል። 

መንግስት ከፍተኛ ወጪ አውጥቶ የሚገነባቸውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን ህብረተሰቡ ሊጠብቃቸው ይገባል ሲሉም ዶክተር ኢንጂነር ሐብታሙ ኢተፋ ገልፀዋል። 

የዞኑ እና የከተማው  አስተዳደር የውሃ ፕሮጀክቱን አቅም ለማጎልበት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባም ሚኒስትሩ አሳስበዋል። 

የክልሉ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አክሊሉ አዳኝ በበኩላቸው በክልሉ 1 ነጥብ 2 ማሊዮን የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በ14 ከተሞች የንፁህ መጠጥ ውሃ ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የዲላ ከተማ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀከት  በ348 ሚሊዮን 89 ሺህ ብር ወጪ የተገነባ ሲሆን ከ192 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም የቢሮው ኃላፊው ተናግረዋል። 

ለፕሮጀክቱ የ59 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የቧንቧ መስመር ዝርጋታ ተከናውኗል ያሉት ኢንጂነር አክሊሉ አዳኝ ለቀጣይ 10 ተከታታይ ዓመታት የከተማውን ነዋሪ ቁጥር ታሳቢ አድርጎ የተገነባ ነው ብለዋል። 

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) ከተማዋ ለዘመናት የቆየ የውሃ እጥረት እንደነበረባት ጠቅሰው አዲሱ ፕሮጀክት 6 ሺህ 500 ሜትር ክዩብ መያዝ የሚችል 2 ሪዘርቫየሮች ያሉት መሆኑ የከተማውን ህብረተሰብ የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር እንደሚቀርፍም ጠቁመዋል። 

የዲላ ከተማ ከንቲባ አቶ ዳንኤል ሽፈራው በመርሃ ግብሩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።