የሕዳሴ ግድብ የዘመናት የቁጭት ምዕራፍ ተዘግቶ የማንሠራራት ምዕራፍ የሚጀምርበት ነው
ጳጉሜን 4/ 2017 ዓ.ም
የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለምረቃ መብቃቱን አስመልክተው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ÷ የሕዳሴ ግድብ የዘመናት የቁጭትና የታሪክ ኩስምና ምዕራፍ ተዘግቶ የማንሠራራት ምዕራፍ ጅማሮ በታላቅ ብሔራዊ ድልና ኩራት የተበሰረበት መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ባስተላለፉት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ÷ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የዘመናት ቁጭትን የሰበረ የኢትዮጵያውያን የአንድነትና ትብብር ውጤት ነው፡፡
የሕዳሴ ግድብ ከኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫነት ባለፈ የሕዝብ ተስፋ አቃፊ፣ የሀገር ሉዓላዊነት ማረጋጋጫ እና የኢትዮጵያን ቀጣይ የመወሰን ጥንካሬ የሚያጎናጽፍ መሆኑን አውስተዋል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በበኩላቸው÷ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የመላ ኢትዮጵያውያን የሕብረት እና የአንድነታችን ማረጋገጫ፣ የአብሮነታችን ምስክር እንዲሁም የእድገታችን መዳረሻ መንገድ ነው ብለዋል፡፡
ግድቡ የኃይል አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት የሚፈታ እና የሕዝባችን ጥቅም የሚያረጋግጥ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት መሆኑን አንስተዋል።
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ÷ ዛሬ የብዙ ትውልዶች ሕልም፣ የብዙ ዓመታት ውጣ ውረድና የብዙ ኢትዮጵያውያን ተስፋ ፍሬ ያፈራበት ታሪካዊ ቀን ነው ብለዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)÷ የኢትዮጵያውያን የዘመናት ቁጭት የሆነው ሕዳሴ ግድብ በቆራጥ ሀገር ወዳድ መሪና ሕዝብ ወደ ድል ተሸጋግሯል ብለዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ÷ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ የማንሰራራት ጅማሮ፣ የአይበገሬነት ተምሳሌት፣ የአንድነትና ፅናት ምልክትና የጋራ ታሪክ ዐሻራ መሆኑን አውስተዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ ÷ አይቻልም የተባለውን እንደሚቻል፤ አንድ አይደሉም ላሉን ደግሞ አንድ ላይ ቆመን ሕዳሴን ገንብተን አሳይተናል ሲሉ ገልጸዋል።
ዛሬ በመንሠራራት ላይ የምንዘራው የብልጽግና ዘር ነገ የሕዝቦችን የጋራ ራዕይ እና የተግባር ፍኖተ ካርታ የሚያበቅል ነው ያሉት ደግሞ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ናቸው፡፡
Copyrights 2021. . All Rights Reserved.
Developed by NATNAEL ABATE