"የከተሞች አገልግሎት አሰጣጥን የማዘመን ተግባር በልዩ ትኩረት ሊመራ ይገባል" ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
የተመረጡ ከተሞችም በአጭር ጊዜ የዲጂታል አገልግሎትን ለመጀመር አፅንኦት ሊሰጠው እንደሚገባም ተጠቁሟል
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በመድረኩ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት በ2018 በጀት ዓመት በተግባርም በዕይታም ስራዎች በልዩ ትኩረት የሚመሩበት እንደሆነም ጠቁመዋል።
ለከተሞች እውቅና ከተሰጣቸው በኃላ የችግር፣ የኪራይ ሰብሳቢነት እና የህብረተሰቡ ምሬት ምንጭ እየሆኑ ይገኛል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ችግር በመቅረፍ ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆኑ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በክልሉ የሚገኙ ከተሞችን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ አመላክተዋል።
ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግና ለማዘመን ከተለመደው የአገልግሎት አሰጣጥ ማላቀቅ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ አገልግሎት አሰጣጣቸውን ማቀናጀት እንደሚገባም ገልፀዋል።
ለረዥም ጊዜ እየተንከባለለ የሚገኘውን የካዳስተር ተግባር በአጭር ጊዜ ከማጠናቀቅ ባሻገር በከተሞች የሚስተዋሉ ችግሮችን እየለዩ ለመቅረፍ አፅንኦት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቅሰዋል።
የክልሉ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው የከተሞች አገልግሎት አሰጣጥ ውስብስብና ብዙ ውጣ ውረድ የበዛበት መሆኑን ገልፀው ለዚህም ዋነኛ ምክንያት በቴክኖሎጂ ያልተደገፈ መሆኑን አመላክተዋል።
በከተሞች እየተመዘገበ ያለውን ፈጣን ዕድገትን የሚመጥን የማዘጋጃ ቤታዊ አገልገሎት አሰጣጥ ማቅረብ አለመቻሉን የገለፁት የቢሮው ኃላፊ ወቅቱን የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት መትጋት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ከተሞች የአገልግሎት አሰጣጥን ከማዘመን ባሻገር የአንድ መስኮት አገልግሎት ለመስጠት አፅንኦት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥን በክልሉ 9 ከተሞች ዲጂታላይዝ ለማድረግ መታቀዱን የገለፁት አቶ ብርሃኑ የዲላ ከተማ ቀድሞ ማጠናቀቁን ጠቅሰው ሌሎች በአጭር ጊዜ እንዲጀምሩ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በቀጣይ በወላይታ ሶዶ፣ አርባምንጭ ፣ ሳውላ፣ ጂንካ፣ ካራት፣አረካ፣ቦዲቲ እና ይርጋጨፌ ከተማ ላይ የኢኮዲንግ፣የስካኒንግ፣ሀርድ ዌር ግብዓቶችን የሟሟላት እንዲሁም የክላውድ ሰርቨር እና የኢንተርኔት ሰርቪስ የመግዛት ስራ መከናወኑንም አቶ ብርሃኑ አብራርተዋል።
ለስራው መሳካት የድርሻቸው የተወጡ አካላትንም የቢሮው ኃላፊ አመስግነዋል።
የዲላ ከተማ ከንቲባ መስፍን ደምሴ (ዶ/ር) የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት የከተማውን የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ችግር በመቅረፍ ለማዘመን በተሰራ ስራ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
Copyrights 2021. . All Rights Reserved.
Developed by NATNAEL ABATE