ዮ.. ዮ ..ጋሞ ማስቃላ የጋሞ ህዝብ የሰላም፣ የፍቅር እና የአንድነት መገለጫ የሆነው ዮዮ ማስቃላ የዘመን መለወጫ በዓል "ዱቡሻና ዱቡሻ ወጋ ለዘላቂ ሰላማችን እና ልማታችን " በሚል መሪ ቃል ከመስከረም 10-12/2018 ዓ.ም ይከበራል። በዓሉም በአርባምንጭ ከተማ በህዝቦች አብሮነት፣ አንድነትና በኅብረ-ብሔራዊነት ይበልጥ አሸብሮቆ በታላቅ ድምቀት ይከበራል!! በወርሃ መስከረም የሚከበረው የ' ዮ' ጋሞ ማስቃላ ዘመን መለወጫ በዓል በጉጉት ተጠባቂና በሀገራችን ልዩ ድባብ ከሚስተዋልባቸው በዓላት አንዱ ነው፡፡ በጋሞዎች ‹ዮ '' ማስቀላ› ማለት ‹መስቀል እንኳን ደህና መጣልን› ማለት ነው፡፡ የሕዝቡ የዘመን መለወጫ በመሆኑ በልዩ ድምቀትም ይከበራል፡፡ ለዮ ማስቃላ በዓል ሲባል እናቶችና አባቶች እቁብ በመጣል ዝግጅቱን ይጀምራሉ፡፡ እናቶች ለማስቃላ ቡላ፣ ወተት፣ ቂንጬ ለመሥራት የሚያገለግለውን ገብስ፣ በቆሎ፣ ቅቤና ቅመማ ቅመም ለማዘጋጀት ዓመቱን ሙሉ እቁብ ሲጥሉ ይከርማሉ፡፡ አባቶች ደግሞ የሚጥሉት እቁብ ለሰንጋ መግዣነት የሚውል ነው፡፡ ወጣቶች ለደመራ እንጨት በመሰብሰብና በማሰናዳት፣ ለከብቶች ሳር አጭዶ በመከመርና ጉልበት የሚጠይቁ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ያግዛሉ፡፡ "ዮ "ማስቃላ በጋሞ ብሔረሰብ በኩል ሁሉም ቂሙን ረስቶ በእርቅ፣ በይቅርታ፣ በሠላምና በአብሮነት ከክፉ ተግባርና ሐሳብ ወጥቶ በአዲስ መንፈስ የሚታደስበት ጊዜ ነው፡፡ የ"ዮ "ማስቀላ በዓል በጋሞዎች ምድር ረዘም ላለ ጊዜ ይዘልቃል፡፡ ዝግጅቱ ለሰዎች ብቻ ሳይሆን እንስሳትንም በማሰብ የሚከናወን ነው፡፡ በበዓሉ ወቅት ሁሉም ወደ በዓሉ የሚሄዱ በመሆኑ ከብቶች የሚመገቡት ድርቆሽ ቀደም ብሎ ይዘጋጃል፡፡ ከዚህ ውጭ በበዓሉ ወቅት የሚግጡት ሰፊ ቦታ/ ካሎ/ ለግጦሽ ተካልሎ ይቀመጣል። ሕጻናት ከብቶቹን ወደ ግጦሽ መስክ ካሰማሩ በኋላ ‹‹ለአዲሱ ዓመት እንኳን አደረሰን፤ እንኳን መስቀል በሰላም መጣልን፤… … በደስታ አደረሰን እያሉ ያከብራሉ ።
Copyrights 2021. . All Rights Reserved.
Developed by NATNAEL ABATE