አንድነትን የሚያጠናክሩ እና የጋራ ትርክትን የሚያጎለብቱ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን አጉልቶ ማውጣትና ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል፦ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አንድነትን የሚያጠናክሩ እና የጋራ ትርክትን የሚያጎለብቱ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን አጉልቶ ማውጣትና ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ተናገሩ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኘው የባስኬት ሕዝብ ዓመታዊ የምስጋና በዓል "ሾላኣ-ካሻ" በባህላዊ ክዋኔዎች ታጅቦ በላስካ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ጥላሁን ከበደ፣ በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የ''ሾላኣ ካሻ'' በአል እርስ በእርስ መመሰጋገንን፣ ቅን አስተሳሰብን እና ዕርቀ-ሰላምን የሚያበረታታ ነው ብለዋል።
እንደ 'ሾላዓ ካሻ' ያሉ የሀገር ሀብት የሆኑ በርካታ ባህሎችና እሴቶች አሉን ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ በእነዚህም የህዝቦችን አንድነት የሚያጠናክሩ እና የጋራ ትርክትን የሚያጎለብቱ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን አጉልቶ ማውጣትና ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል ነው ያሉት።
የባስኬቶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ፍሬው ፍሻለው በበኩላቸው የባስኬት ሕዝብ ለዘመናዊው አስተዳደር ስርዓት ጠቃሚ የሆኑ ቱባ ባህሎችና ሀገር በቀል እሴቶች እንዳሉት አንስተዋል።
የ''ሾላዓ ካሻ'' አመታዊ የምስጋና በዓልም በውስጡ በርካታ እሴቶች እንዳሉት አንስተው፣ ከእሴቶቹ አንዱ የህዝቦች አንድነትና አብሮነት እንዲጠናከር ማድረግ ነው ብለዋል።
በዓሉ አድጎና ጎልብቶ ለትውልድ እንዲሻገር የዞኑ ህዝብ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
Copyrights 2021. . All Rights Reserved.
Developed by NATNAEL ABATE