• Call Us
  • +251..........

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ መልእክት

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የየራሳቸው የሆነ አኩሪ ባህል፤ታሪክና መልአከዓ-ምድራዊ አሰፋፈር፤ የሥነልቦና አንድነት፤ በጋራ ያፈሩት ሀብትን የሚጋሩ እንዲሁም የመልማት ፍላጎት ያላቸው ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በነሐሴ 13 ቀን 2015 .ም ከቀድሞው የደቡብ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በአዲሱ አደረጃጀት የተመሰረተ ክልል ነው፡፡ በክልሉ 32 ነባር ብሄረሰቦችና የተለያዩ ህዝቦች በመፈቃቀድና በመተጋገዝ የሚኖሩበት በተፈጥሮ የበለጸገና  በፍጥነት የመልማት እድል ያለው ክልል ነው፡፡ ሰፊ የኢንቨስትመነት አማራጮች፤ እምቅ ሀብት እንዲሁም ይህን ሀብት ለማልማት የሚችል በስራ ታታሪነቱ የሚጠቀስ የሰው ሃይል የሚገኝበትና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች የሚያቀላጥፉ የመሰረተ ልማትና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የሚያግዝ ዘመናዊ የአሰራር ስርአት የተገነባበት ክልል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አለምን የሚያስደምሙ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ የቱሪዝም መዳረሻዎች የሚገኙበት ቀጠና ነው፡፡  

ክልሉ በአዲስ ሲደራጅ ያለውን የዜጎችንና የማህበረሰብ ብዝሃነት፣ አብሮነትና የመከባበር እሴትን መሰረት በማድረግ ዘላቂ ሰላምና ዕድገት በክልሉ ያለውን የማህበረሰብ ብዝሀነትና እምቅ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብቶችን በተሻለ አደረጃጀትና አስተዳደር በመጠቀም የጋራ ልማት፤ የዴመክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና የመልካም አስተዳደር ስኬቶችን ማረጋገጥ በመሻቱ ነው፡፡  የአገልግሎት ተደራሽነትን በማረጋገጥ፣ በእኩልነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ አሠራርን እውን በማድረግ ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ ዕድገት ጉልህ ድርሻ ያለው ሆኖ እንዲወጣ የተደራጀ ክልል ነው፡፡ ይሕን ሁለንተናዊ ብዝሀነት በመጠቀም ክልሉ የሚጠበቁበትን ክልላዊና ሀገራዊ ውጤቶች በአጭር ጊዜ ለማስመዝገብ የህብረተሰብ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ መሄድ ይኖርባታል፡፡

ከዚህ አንጻር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳች ቢሮ ጠንካራና በጥናትና ምርምር የታገዘ አካታች የኮሚኒኬሽን አሰራር ስርዓት በመዘርጋት ጥራት ያለው፣ ቀልጣፋ እና አስተማማኝ የኮሚኒኬሽን አገልግሎት በመስጠት በመረጃ የበለጸገ ህብረተሰብ እንዲፈጠርና የክልሉ ገጽታ እንዲገነባ የማስቻል ተልእኮ የተሰጠው በመሆኑ ህዝብን በማንቃት የመንግስት መረጃዎችን በመስጠት፤ ህዝብም በልማቱና በስርአት ግንባታው የበኩሉን ሚና ይጫወት ዘንድ የላቀ ኃላፊነት ይጠበቅበታል፡፡

ቀልጣፋ የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ስርዓትን በመፍጠር መላውን ህዝብ ለማነጋገር እና የህዝቦችን ተሳትፎ ለማሳደግ፤ የመንግስት መረጃዎችን በማግኘት ረገድ ለህዝቦች እና የህብረተሰብ ክፍሎች እኩል እድሎች እንዲፈጠሩ ማመቻቸት፤ ቀልጣፋና ውጤታማ የግንኙነትና የመረጃ ስርዓት በማስቀጠል ብሔራዊ ብሎም ክልላዊ አንድነትና መግባባትን ለመፍጠር፣ የዴሞክራሲ ባህልን ለማጠናከር ስትራቴጂካዊ አመራር ለመስጠት፤ ጠንካራ የዲጂታል ሚዲያ ማዕቀፍ፣ ኔትወርክ እና መዋቅር በመፍጠር የመንግስትን አጀንዳዎች  ተደራሽነት ይበልጥ በማሳለጥ የክልሉ ማህበረሰብ የሚጠብቀውን ልማትና የመልካም አስተዳደር ትሩፋቶች በአጭር ጊዜ ይሳኩ ዘንድ ተቋሙ ጥረቶችን እያደረገና በዚህ የአዲሱ ክልል ግንባታ የራሱን መሰረት እያስቀመጠ የሚገኝ  ነው፡፡

የመገናኛ ብዙሀንና የመረጃ ነጻነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 የተደነገገውን የህዝብን መረጃ የማግኘት መብት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግና ዘመኑ የደረሰባቸውን ቴክኖሎጅዎች በተለይ ወጣቱን ጨምሮ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ዲጅታል ሚዲውን የሚጠቀም በመሆኑ ወቅታዊ፤ ትክክለኛና ፈጣን የመረጃ ፍላጎቶችን ለማሟላትና የመንግስት አጀንዳዎችን፤ ፕሮግራሞችና እቅዶችን ብሎም የክልሉን ጸጋዎችና ሀብቶች ለማስተዋወቅ በቢሮው ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን የክልላችን ነዋሪዎች፤ ወዳጆቻችና አጋሮቻችን የክልሉን አዳዲስና ወቅታዊ መረጃዎች ለማግኘት ቀድሞ ከምንጠቀምባቸው ሚዲዎች በተጨማሪ በቅርቡ ያለማነውን ዌብ ሳይት እንድትጠቀሙ እንጋብዛለን፡፡